ፓርላማውን ያስቆጣና የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ቀውስ የተመለከተ ሪፓርት ቀረበ

Source: https://kalitipost.com/%E1%8D%93%E1%88%AD%E1%88%8B%E1%88%9B%E1%8B%8D%E1%8A%95-%E1%8B%AB%E1%88%B5%E1%89%86%E1%8C%A3%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9A%E1%8B%AB%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%88%B6%E1%88%9B%E1%88%8C/

የፓሊስ ኮምሽነሩ ክልሎቹ ተጠርጣሪዎችን አሳልፈው እየሰጡ አይደለም ብለዋል

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ከአንድ ወር ተኩል በፊት ያካሄደውንና በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን የሚመለከተው ሪፓርት በዛሬው ዕለት አዳምጧል። በሪፓርቱ ለግጭቱ በወቅቱ ምላሽ በመስጠትና አጥፊዎችን ለፍርድ በማቅረብ ረገድ የፌደራል መንግሥት ድክመት ነበረበት በሚል ተተችቷል።

በፓርላማው የተዋቀረው የሱፐርቭዥን ቡድን ከጥቅምት 25 እስከ ህዳር 2 ቀን 2010 በሶስት አቅጣጫዎች በተመረጡ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ በ16 ወረዳዎች የመስክ ምልከታ ማካሄዱንና ለሚመለከታቸው አካላት በቃልና በጱሁፍ ሪፓርቱን ማቅረቡንና ለፓርላማው ግን በይፋ ባልገለጰው ችግር ምክንያት በወቅቱ አለማቅረቡን አስረድቷል።

በፓርላማው ሱፐርቭዥን ከተለዩት ችግሮች መካከል በግጭቱ የዜጎች ሕይወት ንብረት መጥፉቱን፣ ጉዳት ከመድረሡ ባሻገር ከተፈናቀሉ በሀላ ለረጅም ግዜ ያለአስተዋሽ መቀመጣቸው በመንግስት ላይ ተስፋ መቁረጥና አመኔታ ማጣት ማስከተሉ ገልጷል። ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች በሚፈለገው ደረጃ አለመቅረቡን፣ የትምህርት የጤና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ ተነስቷል።

ግጭቱ ታህሳስ 2009 መጀመሩን ግን እስካሁን መቀጠሉ በሪፓርቱ በአሳሳቢነቱ ተነስቷል።

የፓርላማ አባላቱ ሪፓርቱ ከተሰራ ከአንድ ወር ተኩል በሀላ መቅረቡ እጅግ የዘገየ ብለውታል። አያይዘውም የፌደራል መንግስት ለሰብአዊ ቀውሱ የሰጠው ምላሽ ዘገምተኛ ነው በሚል የወቀሱ ሲሆን ችግሩን የፈጠሩ ግለሰቦች ለምንድነው ለፍርድ የማይቀርቡት በማለት መረር ያሉ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።

ፓርላማውን የመሩት የሕዝቤ ጥቅም ተነክቷል ብለው መልቀቂያ ያስገቡትና በሽምግልና የተመለሱት አቶ አባዱላ ገመዳ ሲሆኑ በአስረጅነት ምክትል ጠ/ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ አቶ ከበደ ጫኔ የአርብቶአደር ሚኒስትር፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የመከላከያ ሚኒስትር፣ አቶ አሰፋ አብዩ የፌደራል ፓሊስ ኮምሽነር፣ አቶ ምትኩ ካሳ የፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽነር ተገኝተዋል።

የፓሊስ ኮምሽነሩ ተጠርጣሪዎችን መያዝ መጀመራቸውን ጠቅሰው በሁለቱም ክልሎች በኩል ተጠርጣሪዎችን አሳልፎ በመስጠት በኩል ችግር እንደገጠማቸው ለፓርላማው ተናግረዋል።

ስብሰባው ዛሬ ከሰአትም ይቀጥላል። Kaliti Post

Share this post

One thought on “ፓርላማውን ያስቆጣና የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ቀውስ የተመለከተ ሪፓርት ቀረበ

Post Comment