ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ተወያዩ

Source: https://fanabc.com/2019/09/%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%8B%9A%E1%8B%B3%E1%8A%95%E1%89%B5-%E1%88%B3%E1%88%85%E1%88%88%E1%8B%88%E1%88%AD%E1%89%85-%E1%8A%A8%E1%89%B0%E1%88%98%E1%8B%B5-%E1%8B%8B%E1%8A%93-%E1%8D%80%E1%88%83%E1%8D%8A/

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ተወያዩ።

ውይይቱ ከኒውዮርኩ የተመድ 74ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የተካሄደ ነው።

ፕሬዚዳንቷ በዚህ ወቅት ባለፈው አንድ አመት በኢትዮጵያ የተካሄዱ ለውጦች ባላቸው ጠቀሜታ ዙሪያ ማብራሪያ አድርገዋል።

ለደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት መተግበርና በኤርትራና ጂቡቲ መካከል ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገው ጥረት እንዲሳካ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗንም ፕሬዚዳንቷ በዚህ ወቅት ገልጸዋል።

አያይዘውም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ወሲባዊ ጥቃትና ጾታዊ ትንኮሳ ለመከላከል በዋና ፀሃፊው የሚመራው ቡድን አባል ይሆኑ ዘንድ የቀረበላቸውን ጥያቄ እንደሚያጤኑትም ጠቅሰዋል።

የተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ለተካሄዱ ማሻሻያዎች እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በደቡብ ሱዳን በአሸማጋይነት ለተጫወቱት ሚና ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

አያይዘውም ይህን መሰሉ ሂደት በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ውስጥ ሊደገም ይገባል ማለታቸውን በተመድ የኢትዮጵያ ተጠሪ የፌስ ቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘ ዜና ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአፍሪካ የሰላም፣ የደህንነትና የልማት ጉዳይ ላይ በመከረው መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።

መድረኩ በጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል የተመራ ሲሆን፥ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ተካፍለውበታል።

ውይይቱ በዋናነት በሰላም፣ ደህንነትና የልማት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.