ፕሬዚዳንት ትራምፕ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪያቸውን ጆን ቦልተንን ከስልጣን አነሱ

Source: https://fanabc.com/2019/09/%E1%8D%95%E1%88%AC%E1%8B%9A%E1%8B%B3%E1%8A%95%E1%89%B5-%E1%89%B5%E1%88%AB%E1%88%9D%E1%8D%95-%E1%89%A5%E1%88%84%E1%88%AB%E1%8B%8A-%E1%8B%A8%E1%8B%B0%E1%88%85%E1%8A%95%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8A%A0/

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 6 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪያቸውን ጆን ቦልተንን ከስልጣን አነሱ።

ፕሬዚዳንቱ የደህንነት አማካሪያቸው ከስልጣን እንዲለቁ እንደነገሯቸው በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ጆን ቦልተን በነጩ ቤተ መንግስት መቆየት እንደሌለባቸው መናገራቸውን አስታውቀዋል።

አያይዘውም ጆን ቦልተን በሚያቀርቡት ምክረ ሃሳብ ዙሪያ አለመግባባታቸውንም ጠቅሰዋል።

የእርሳቸውን ምትክም በቀጣዩ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርጉም ነው ትራምፕ ያስታወቁት።

ጆን ቦልተን በበኩላቸው ከትራምፕ የትዊተር ጽሁፍ በኋላ ከሃላፊነታቸው እንደተነሱ አስታውቀዋል።

እርሳቸውም በትዊተር ገጻቸው ሃላፊነታቸውን እንዲለቁ ጥያቄ እንደቀረበላቸውና ያንን ተግባራዊ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጅ “በሆነው ነገር ላይ የምለው ነገር ይኖረኛል” ማለታቸውም ተሰምቷል።

ቢቢሲ ከኋይት ሃውስ ምንጮች አገኘሁት ባለው መረጃ ቦልተን ከፕሬዚዳንቱ ፅህፈት ቤት ባፈነገጠ መልኩ ስራቸውን ሲሰሩ እንደነበር አስነብቧል።

እንደ ምንጮቹ ገለጻ አማካሪው ፕሬዚዳንቱ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ሃሳብ ከማቅረብ ይልቅ በራሳቸው መንገድ ነገሮችን ይከውኑ ነበር።

ይህም ከፕሬዚዳንቱና ከመላው የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ሰፋ ያለ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗልም ነው ያሉት ምንጮቹ።

ጆን ቦልተን ከፈረንጆቹ ሚያዚያ ወር 2018 ጀምሮ የፕሬዚዳንቱ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።

ከእርሳቸው ቀደም ብሎ ማይክል ፍሊን እና ማክማስተር በዚህ ሃላፊነት ላይ ቆይተዋል።

አዲሱ ብሄራዊ የደህንነት አማካሪ እስከሚሾም ድረስም ቻርልስ ኩፐርማን በጊዜያዊነት ቦልተንን ተክተው ይሰራሉ።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.